ሰማያዊ ትንቢታዊ ሕዝብ ማስነሳት ነው
በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና።በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም። በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ አመስግኑ።
ኤፌ 5፡18-20
የጽዮን ድምፅ አገልግሎት ዳይሬክተር
ሰማያዊ ትንቢታዊ ሕዝብ ማስነሳት ነው።
ቅዱሳን ዘወትር በምስጋና እና በመንፈስ እንዲሞሉ ማገልገል ነው።
የሰማያዊ መንግስትን ሕይወት እና ክብር መግለጥ ነው።
የጽዮን ድምፅ አገልግሎት ሁለት የአገልግሎት ክፍሎችን በስሩ የያዘ ሲሆን እነርሱም የሙዚቃ እና የስነ-ጥበብ አገልግሎት ናቸው። ይህ አገልግሎት በዋናነት የሚመደበው ትንቢታዊ አገልግሎት ውስጥ ሲሆን ዋና ተግባሩም ቅዱሳንን ማነጽ፣ ማበረታታት እና ማጽናናት ነው።
በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በክርስቶስ ከተቀበልናቸው ሶስት ቅባቶች (ነገስታት፣ ካህናት እና ነቢያት) መካከል አንዱ የትንቢት (የነብያት) ቅባት ነው። ይህም ቅባት የእግዚአብሔርን መንግስት ኃይል እና ክብር እንድንለማመድ የሚያደርገን ቅባት ነው። ትንቢት የእግዚአብሔርን ሐሳብ (ቃል) በልብ የመሸከም እና በአንደበት የማወጅ ሕይወት ሲሆን ከእግዚአብሔር ቃል ኃያልነት የተነሳ እኛን እንደ ቃሉ የመገንባት እና የማነጽ መንፈሳዊ ኃይል አለው። ስለዚህም እግዚአብሔር ሕዝቡን ትንቢታዊ ሕዝብ አድርጎ መገንባት ይፈልጋል።
ህዝብ (Nation) ማለት አንድ አይነት ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግ እና ስርዓት የሚጋራ ማህበረሰብ ማለት ነው። የትንቢት አገልግሎት ሰማያዊ ሕዝብን (Heavenly Nation) ከመገንባት አንጻር ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። ትንቢት ቅዱሳን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ባለ ቋንቋ እንዲዋጁ እና እንዲገነቡ የማድረግ ከፍተኛ ኃይል አለው። የጽዮን ድምጽ አገልግሎትም ከጌታ በተቀበለው ልዩ ጸጋ እና ጥበብ ቅዱሳንን በጽዮን ቋንቋ እና ባህል ለመገንባት የአገልግሎት ኃላፊነት ድርሻን ተሸክሞ በማገልገል ላይ ይገኛል። ይህም ቅዱሳን የሰማያዊ መንግስትን ሕይወት እና ክብር እንዲገልጡ ያስችላቸዋል።
የሙዚቃ አገልግሎት ክፍል የጽዮን ድምጽ አገልግሎት አንዱ ክንፍ ሲሆን ትንቢታዊ የሆነን የዝማሬ አገልግሎትን የማገልገል ኃላፊነትን የተሸከመ ነው። ይህ አገልግሎት ክፍል ልዩ የዝማሬ እና የሙዚቃ ተሰጥኦ ያላቸውን አገልጋዮች የሚያቅፍ ሲሆን ዋና ግቡም የጊዜውን ትንቢታዊ ዝማሬዎችን ከመንፈስ ቅዱስ ተቀብሎ በማገልገል ቅዱሳንን ማነጽ፣ ማበረታታት እና ማጽናናት ነው። “በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና።በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም። በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ አመስግኑ።” ኤፌ 5፡18 -20 (አ.መ.ት) ዝማሬ በመንፈስ የምንሞላበት ሰማያዊ ደጅ ነው። ቅዱሳን በመንፈስ ቅዱስ ሲሞሉ ትንቢታዊ ቃልን ከመንፈስ ቅዱስ ተቀብለው በሕይወታቸው ላይ እንዲያውጁ ያስችላቸዋል፤ ይህም የእግዚአብሔርን ኃይል በሕይወታቸው እንዲለማመዱ እና እንዲገለጥ እንዲሁም በክርስቶስ በተሰጣቸው የመንግስቱ ሕይወት ከክብር ወደ ክብር ከፍ እያሉ እንዲሄድ ያደርጋቸዋል። በመጨረሻው ዘመን የእግዚአብሔር ሐሳብ ስጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሱ ማፍሰስ እና ወንዶች እና ሴቶች ልጆቹ ትንቢት ሲናገሩ ማየት ነው። ይህም የእግዚአብሔር መንግስት እና ሕዝብ በትውልድ መካከል በኃይል እና በታላቅ ክብር የሚገለጥበት ሰማያዊ ምስጢር እና ጥበብ ነው። የዚህም አገልግሎት ዋና ኃላፊነት ትንቢታዊ ሕዝብን ማስነሳት ነው።
የስነ-ጥበብ የአገልግሎት ክፍል የጽዮን ድምጽ አገልግሎት ሁለተኛው ክንፍ ሲሆን ሰፊ እና ዘርፈ ብዙ የአገግሎት ኃላፊነቶች የያዘ ነው። የአገልግሎት ክፍሉ ግጥም፣ ድራማ፣ ስዕል፣ ማይም፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እና አገልግሎቶችን ያካትታል። የመሳሰሉትን ልዩ የጥበብ አገልግሎቶችን ያካትታል።
መፅሐፍ ቅዱሳችን በውስጡ ብዙ ስነ-ጥበባዊ መልዕክቶችን የያዘ ሲሆን በዋናነት በትንቢታዊ አገልግሎት ውስጥ ጉልህ በሆነ ሚና ሲገለጥ እናስተውለዋለን። መንፈስ ቅዱስ ይህን ጸጋ ልዩ በሆነ መንገድ ትውልድን የሚመጣውን ዘመን ለማመልከት፣ ለማጽናናት፣ ለመምከር እና ቅዱሳንን ለማጽናት ይጠቀምበታል።
የስነ-ጥበብ አገልግሎት የእግዚአብሔር _ መንግስትን እውነታዎች ምሳሌያዊ፣ ቀላል፣ ተግባራዊ ሊሆን በሚችል እና ነገን አመልካች በሆነ መንገድ በቅዱሳን ሕይወት ውስጥ የማስረጽ ወይም የመመስረት ከፍተኛ አቅም አለው። ይህን ለመረዳት የብሉይ ኪዳንን እና የአዲስ ኪዳንን መገለጥ መመልከት ይቻላል። እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን የሚገለጠውን የክርስቶስን መልክ በሚገባ መረዳት እንድንችል በብሉይ ኪዳን ውስጥ በምሳሌነት እና በጥላነት የገለጠበት መንገድ ፍጹም አስደናቂ እና ጥልቅ ጥበብ የታየበት ነው፡፡ ይህም የአገልግሎት ክፍል በተመሳሳይ መልኩ ልዩ በሆነ ጥበብ የሰማያዊውን መንግስት ሕይወት እና ክብር ለቅዱሳን የመግለጥ ኃላፊነትን ተሸክሟል። ይህም የማይታየውን የማሳየት፣ የነገውን ዛሬ የመግለጥ፣ እውነትን በምሳሌ የማስረዳት አስደናቂ ትንቢታዊ አገልግሎት ነው፡፡
የስነ-ጥበብ የአገልግሎት ክፍል
በክራይስት ሲቲ ቸርች፣ በጽዮን ድምፅ አገልግሎት በግንቦት ወር የሚዘጋጅ በአይነቱ ልዩ የሆነ ዓመታዊ የምስጋና ኮንፍራንስ ሲሆን በዝማሬ፣ በስነ-ጥበብ እና ልዩ በሆነ መስዋዕት እግዚአብሔርን የምናከብርበት ድንቅ በዓል ነው።