የመንግስቱን መልዕክት ለትውልድ ሁሉ ማድረስ
ለለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።
የማቴዎስ ወንጌል 24:14
የመንግስቱ መልዕክተኞች አገልግሎት ዳይሬክተር
የመንግስቱን መልዕክት ለትውልድ ሁሉ ማድረስ!
የመንግስቱን መልዕክት ለቅዱሳን እና ለትውልድ ሁሉ ተደራሽ ለማድረግ ለተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እድል መስጠት።
በዘመኑ ያሉ የመገናኛ ብዙሃንን የመንግስቱን መልዕክት በፅሁፍ ፣ በድምፅ እና በምስል ለማስራጨት ፣ ለማስፋፋት እና ይፋ ለማድረግ መጠቀም።
የመንግስቱን መልዕክት ለትውልድ ሁሉ ማድረስ!
የህትመት አገልግሎት ክፍል በመንግሥቱ መልዕክተኞች አገልግሎት ስር የሚገኝ አገልግሎት ክፍል ሲሆን የመንግስቱን መልዕክት በህትመት መልኩ የማድረስ ኃላፊነትን የተሸከመ ነው። የዚህ አገልግሎት ክፍል ዋና ግቡ ለቤተክርስቲያን እና ለአገልግሎቶች የተለያዩ የህትመት ስራዎችን ከማከናውን ጀምሮ መልዕክቶችን በፅሁፍ መልክ በማዘጋጀት እና በማተም የመንግስቱን መልዕክት በአለም እንዲዳረስ እና በቅዱሳኑም ዘንድ በሕይወታቸው ዘላቂ ውጤት እንዲኖረው ማድረግ ነው። በዚህ አገልግሎት ክፍል ስር የህትመት ክፍል ፣ የፅህፈት እና ትርጉም ክፍል እንዲሁም የመንግስቱ መፅሐፍት መደብር ይገኛሉ።
ይሄ አገልግሎት ክፍል ለክርስቶስ አካል ትልቅ በረከት የሆነ አገልግሎት ሲሆን በእጃችን ላይ የምናገኘው መፅሐፍ ቅዱስ የዚሁ አገልግሎት ውጤት ማሳያ ነው። መፅሐፍ መልዕክት ከትውልድ ትውልድ እንዲሻገር የሚያደርግ ትልቅ ቅርስ ነው። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ሲታወስ እንዲኖር ይህን በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ጻፈው፤ ኢያሱም መስማቱን አረጋግጥ፤ ምክንያቱም የአማሌቃውያንን ዝክር ከሰማይ በታች ፈጽሜ እደመስሳለሁ” አለው።
ዘፀአት 17:14
አሁንም ሂድ፤ በሰሌዳ ላይ ጻፍላቸው፤ በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ከተብላቸው፤ ለሚመጡትም ዘመናት፣ ለዘላለም ምስክር ይሆናል፤
ኢሳይያስ 30:8
እግዚአብሔር የሰራው ስራ ለዘላለም እንዲታወስ ሲፈልግ በመፅሐፍ እንዲፃፍ ያደርጋል። አምላካችን ሁሌም የማይለዋወጥ አንድ አምላክ ነው። ትናንት በመልካምም ይሁን በመጥፎ ጎዳና ካለፉት አባቶች ከታሪካቸው ተምረን መንገዳችንን እንድናቀና አስተማሪ እና አስፈላጊ የሆኑትን ታሪኮች በመፅሐፍ ቅዱስ ተቀምጠውልናል። 'በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና። '
ሮሜ 15:4
ስጋችን ለመኖር የተለያዩ ነገሮችን እንደሚመገብ ሁሉ መፅሐፍ የነፍስ ምግብ ነው። ሁሉም መፅሐፍት ግን ጤናማ ናቸው ማለት አይቻልም። የትኛውንም መፅሐፍ ከማንበባችን በፊት የማሰብ ፣ የመመልከት እና የመምሰልን መርህ መከተላችንን እርግጠኛ መሆን አለብን። ምክኒያቱም ነፍሳችንን ጤናማ ምግብ ካልመገብናት ትመረዛለች ፤ የተመረዘች እንደሆነ ለስቃያችን ምክኒያት ትሆናለች። ስለዚህ በተቻለን አቅም ሁሉ ከመርዛማ መፅሀፍ ልንከላከላት ይገባል። ይሄን ማድረግ የምንችልበት እንዲሁም በህይወታችን ትልቅ የስኬት ሚስጥር የያዘ የእግዚአብሔር ቃል መርህ አለ። 'የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፤ የኑሯቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሏቸው። '
ዕብራውያን 13:7
የትኛውንም መፅሐፍ ከማንበባችን በፊት ስለ ጸሃፊው በሚገባ ቆም ብለን ልናስብ ፣ የህይወቱን ፍሬ ልንመለከት እና እንደ እግዚአብሔር ቃል ልንመዝን እንዲሁም መልካም ፍሬ አፍርቶ እንደሆነ ልንመስለው ይገባል። መልካምን ፍሬ ያፈሩ አባቶች ያፈሩበትን የእምነት ህይወት በመፅሐፎቻቸው ከትበው አስቀምጠውልናል። ስለዚህ እነሱን መምሰል እና ትናንት እነሱ በተራመዱበት የእምነት ጎዳና በማስተዋል መራመድ ከቻልን እነሱ ያፈሩትን የህይወት ፍሬ ማፍራት እንችላለን።
ኦዲዮ-ቪዡዋል አገልግሎት ክፍል በመንግሥቱ መልዕክተኞች አገልግሎት ስር የሚገኝ አገልግሎት ክፍል ሲሆን የመንግስቱን መልዕክት በምስል ፣ በድምፅ ቅጂ እና በቪዲዮ ለትውልድ ሁሉ የማድረስ ኃላፊነትን የተሸከመ ነው። የዚህ አገልግሎት ክፍል ዋና ግቡ የአየር ሞገዶችን በመጠቀም የመንግስቱን መልዕክት ሳቢ እና ለመረዳት ቀላል አድርጎ በምስል ፣ በድምፅ ቅጂ እና በቪዲዮ መልክ በማዘጋጀት እና በማሰራጨት ትልቅ የወንጌል ደጅ መሆን ሲሆን ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ በትንሽ ጉልበት ብዙዎችን መድረስ የምንችልበት ፣ በየቤቱ መልዕክቶቻችን እንዲገቡ የምናደርግበት እና መልዕክቶችን በማጋራት ቅዱሳን የሚዲያ መድረኮችን የመንግሥቱን መልእክት ለማድረስ እንዲጠቀሙ የምናስችልበት ነው። በዚህ አገልግሎት ክፍል ስር የምስል ዝግጅት ክፍል ፣ የድምጽ ቅጂ ክፍል እና የቪዲዮ ክፍል ይገኛሉ።
ቨርቱዋል አገልግሎት ክፍል በመንግሥቱ መልዕክተኞች አገልግሎት ስር የሚገኝ አገልግሎት ክፍል ሲሆን ለተሻለ ቅልጥፍና የሚረዱ የተለያዩ የዲጂታል መድረኮችን ለጌታ ቤት ስራ የማመቻቸት እና የማበልፀግ ኃላፊነትን የተሸከመ ነው። የዚህ አገልግሎት ክፍል ዋና ግቡ ዘመኑ የደረሰበትን እና በጌታ ቤት የሚከናወኑ ስራዎችን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጉ ፤ ጊዜ ፣ ጉልበት እና ወጪን ለመቀነስ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ማመቻቸት እና ማበልፀግ ነው።
1 ዜና መዋዕል 12:32
'ዘመኑን የተረዱና እስራኤላውያንም ምን ማድረግ እንደሚገባቸው የተገነዘቡ የይሳኮር ሰዎች ሁለት መቶ አለቆች፤ በእነርሱም ሥር ሆነው የሚታዘዙ ዘመዶቻቸው። '
ዘመንን መረዳት እና በዘመኑ ምን ማድረግ እንደሚገባ በሚገባ ማስተዋል ገዢ ያደርጋል። በመሆኑም ቤተክርስቲያን ገዢ ሆና መገለጥ እንድትችል በዚህ ዘመን ባለው የቴክኖሎጂ አለም መሪ ሆና መገኘት ይኖርባታል። በተለይም አሁን ያለንበት እና የሚቀጥለው ዘመን ነገሮች ወደ AI (Artificial Intelligence) እየዞሩ ያሉበት እንደመሆኑ ቤተክርስቲያንም ለወንጌል ስራ መጠቀሚያ ለማድረግ እድሉን መጠቀም ይገባታል። በዚህ አገልግሎት ክፍል ስር የሶሻል ሚዲያ ክፍል እና IT Development ክፍል ይገኛሉ።