ቅዱሳን በእግዚአብሔር መንግስት ባለጠግነት ተባርከው፤ እግዚአብሔርን ሲያከብሩ እና ለሌሎች በረከት በመሆን በመልካም ስራ ባለጠጎች ሲሆኑ ማየት
'በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። መልካም እንዲሠሩ፣ ቸሮችና ለማካፈል ፈቃደኞች የሆኑ እንዲሆኑ እዘዛቸው። በዚህ ዐይነት እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው ያከማቻሉ። '
1 ጢሞቴዎስ 6:17-19
የመንግስቱ ባለጠግነት አገልግሎት ዳይሬክተር
ቅዱሳን በእግዚአብሔር መንግስት ባለጠግነት ተባርከው፤ እግዚአብሔርን ሲያከብሩ እና ለሌሎች በረከት በመሆን በመልካም ስራ ባለጠጎች ሲሆኑ ማየት
የእግዚአብሔርን መንግስት የኢኮኖሚ ስርዓት በቅዱሳን ሕይወት እና በቤተክርስቲያን መመስረት እና መገንባት ነው።
የሰማያዊ መንግስትን ሕይወት እና ክብር መግለጥ ነው።
መንግስት ሕዝቡን ወደ ራሱ ዓላማ እና ሃሳብ ለማድረስ፤ ኃይል እና ክብር (ሃብት) በመጠቀም፤ እንዲሁም ስርዓት በመዘርጋት የሚገዛ ስልጣን ያለው አካል ነው። በምድር ላይ ሰው ሰራሽ የሆኑ የተለያዩ የመንግስት አስተዳደር ስርዓቶች አሉ። ሁሉም ለሕዝባቸው ሁለንተናዊ መባረክ ይጠቅማል ብለው የሚያምኑበትን የአስተዳደር (የፖለቲካ) ስርዓት ይዘረጋሉ። ዳሩ ግን የእግዚአብሔር መንግስት በንጉሳዊ አስተዳደር (Kingdom) ስርዓት የሚተዳደር መንግስት ነው፤ ንጉሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
“እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደ ሚወድደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ . . .” ቆላስይስ 1፡13 (አ.መ.ት)
አንድ ንጉሳዊ መንግስት (Kingdom) በውስጡ አራት ክፍለ አካላቶች (Components) ይኖሩታል። እነርሱም ገዢ (ንጉስ)፣ ተገዢ (ሕዝብ) ፣ ግዛት (ምድር) እና ሕግ (የንጉስ ፈቃድ ወይም ንጉሱ ለሕዝቡ ያለው መልካም ሃሳብ እና ዓላማ) ናቸው።
ገዢው (ንጉሱ) ዓላማውን እና ሐሳቡን ለማስፈጸም ይረዳው ዘንድ ሕግን ተጠቅሞ ለሶስቱ ክፍለ አካላት (Components) ስርዓቶችን ይዘረጋል። እነርሱም :-
1.ለገዢ - የፖለቲካ ስርዓት (Political System) 2.ለተገዢ - የማህበረሰብ ስርዓት (Social System) 3.ለግዛት - የኢኮኖሚ ስርዓት (Economic System)
የኢኮኖሚ ስርዓት ማለት መንግስታት በግዛታቸው ውስጥ ያላቸውን ሀብት (Resources)፣ አገልግሎቶች (Services) እና ሸቀጦች (Goods) በመላው ክልላቸው ወይም አገራቸው ውስጥ ለሚኖሩ ሕዝቦቻቸው የሚያደራጁበት (Organize) እና የሚያከፋፍሉበት (Distribute) መንገድ ነው። የዚህም ዋነኛ ዓላማ የሕዝባቸውን ፍላጎት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለማሟላት እና ሕዝባቸው በባለጠግነት ተባርኮ የመንግስታቸውን ክብር እንዲልገጥ በማለም ነው።
እግዚአብሔር መንግስት እንጂ ኃይማኖት የለውም! በብሉይ ኪዳን የሰማያዊ መንግስቱ ጥላ ለነበረችው እስራኤል እግዚአብሔር ንጉስ (ገዢ) ነበር። በመሆኑም እርሱ ባወረሳቸው ግዛት (ምድር) ውስጥ ለሚኖሩት ለሕዝቡ በረከት የሚሰጥበትን ሕግ እና የኢኮኖሚ ስርዓት ዘርግቶ ነበር። በአንጻሩም ይህን ሕግ እና ስርዓት ፈጽሞ ለሚታዘዝ ሁሉ ምን ዓይነት የከበረ የሕይወት ውጤት እንደሚኖረው በግልጽ እንዲህ ሲል ተናግሯል።
“ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ አብዝቶ ስለሚባርክህ፣ በመካከልህ ድኻ አይኖርም፤ ይህ የሚሆነውም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፈጽመህ ስትታዘዝና ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ስትከተል ብቻ ነው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ስለሚባርክህ፣ አንተ ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከማንም አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ እንጂ ማንም አንተን አይገዛህም።” ዘዳ 15፡ 4-6 (አ.መ.ት)
የእግዚአብሔር መንግስት የኢኮኖሚ ስርዓት በራሱ በእግዚአብሔር ኃይል እና ክብር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ከዓለም መንግስታት የኢኮኖሚ ስርዓት ፈጽሞ የተለየ (የተቀደሰ) ነው። ከዚህም የተነሳ ሕዝቡ ለሌሎች በረከት እንዲሆን እና በአህዛብ ሁሉ ላይ ገዢ እንዲሆን አድርጎታል። ለእስራኤል ሕዝብ ከተሰጡት ትዕዛዞች ከዋናዎቹ መካከል ለምሳሌ በኩራት፣ አስራት፣ አባት እና እናትን ማክበር፣ ለድሃ መስጠት (ለመበለት፣ ለደሃ አደግ እና ለመጻተኛ የሚሰጥ) ፣ የፍቅር ስጦታ፣ የእዳ ምሕረት (በሰባት ዓመት አንዴ የሚደረግ)፣ ኢዮቤልዩ (በ 50 ዓመት አንዴ የሚደረግ)፣ ስለት ፣ መስዋዕት . . . ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህን ፈጽሞ ለሚታዘዝ ሁሉ የበረከት ተስፋ አላቸው። ሁሉም ትዕዛዞች እንደየ ባህሪያቸው የተለያየ የበረከት ደጆችን የሚከፍቱ ናቸው። አንዱ ሌላኛውን አይተካም ወይም አንዱ የሌላውን ውጤት ሊሰጥ አይችልም። በሰው አእምሮ ሊመረመር ከማይችለው የእግዚአብሔር የመሪነት ጥበብ የተነሳ እስራኤል ከሕዝቦች ሁሉ ይልቅ የተባረከ እና የበለጸገ ሕዝብ ነበረ።
በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ ኪዳን፤ በጌታችን እና በንጉሳችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔር መንግስት ለትውልድ ሁሉ ተገልጧል። ይህ ሰማያዊ መንግስት በተሻለ ኪዳን እና ክብር፤ ለቅዱሳኑ በረከት የራሱን የኢኮኖሚ ስርዓት ዘርግቷል ። ይህ የኢኮኖሚ ስርዓት መነሻ መሰረቱን ያደረገው በክርስቶስ የመስቀል ላይ የቤዛነት ስራ ነው።ኢየሱስ ክርስቶስ ከድህነት ተቤዥቶናል!
“የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በእርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ።” 2ኛ ቆሮ 8፡9 (አ.መ.ት)
በንጉሳችን እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መንግስት ውስጥ የሁሉ ነገር የባለቤትነት መብት የንጉሱ ሲሆን ኃብቱ ለእኛ ለዜጎቹ ደግሞ የጋራ ኃብት ነው። ንጉሱ በኃብቱ ላይ ባለአደራ ያደረጋቸውን ሰዎች ጌቶች እና ባሮች በማለት በሁለት ይከፍላቸዋል። ይህም በዚህ ዘመን አገላለጽ የንግድ ባለቤት (Business Owner) እና ሰራተኛ (Worker) የምንላቸው ናቸው። የዚህ የአገልግሎት ክፍል ትኩረት፤ ጌቶች እና ባሮች የሆኑ ቅዱሳንን በባለአደራነት የተቀበሉት ኃብት በበረከት እንዲበዛ በእግዚኢአብሔር መንግስት ስርዓት መሰረት ኃብቱን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው ማስታጠቅ ነው። ይህ የአገልሎት ክፍል በውስጡ የንግድ ባለቤቶች ሕብረት (Businessmen 's Fellowship) እና የሰራተኞች ሕብረት (Workers Fellowship) የሚያቅፍ ይሆናል።
1ኛ ጢሞ 6፡17-19 “በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት . . . መልካም እንዲሠሩ፣ ቸሮችና ለማካፈል ፈቃደኞች የሆኑ እንዲሆኑ እዘዛቸው። . . . ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው ያከማቻሉ።” የዚህ አገልግሎት ትኩረት ቅዱሳን በቤተክርስቲያን በኩል የእግዚአብሔርን መንግስት ለማስፋት በሚደረጉ አገልግሎቶች ውስጥ በተሰጣቸው ጸጋ እና የክህነት ጥሪ የሚሰማሩበትን እርሻ ማዘጋጀት ነው። እግዚአብሔር በስራ ዓለም የተሰማሩ ቅዱሳኑ ስራቸውን እንደ እግዚአብሔር መንግስት ካህናት እንዲያገለግሉ ይፈልጋል። ይህ የካህናት ልብ ደግሞ ተባርከው ለመልካም ስራ የሚበዙበትን የበረከት ደጅ ይከፍታል።
በክራይስት ሲቲ ቸርች፤ በመንግስቱ ባለጠግነት አገልግሎት መስከረም ወር ላይ የሚዘጋጅ በአይነቱ ልዩ የሆነ ዓመታዊ ስብሰባ ሲሆን ዓላማውም ቅዱሳንን በእግዚአብሄር መንግስት የፋይናንስ ጥበቦች ማስታጠቅ ነው።